Wednesday, October 14, 2015

አድርሽኝ

ነሐሴ 5 ቀን 2007 ዓ.ም
ምንጭ፡ ማኅበረ ቅዱሳን 
http://eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1953-2015-08-11-05-46-55
በዘአማኑኤል አንተነህ/ከጎንደር ማእክል/
፩.ታሪክ
20አድርሽኝ ታሪካዊ አመጣጡ በጎንደር ከነገሡት ነገሥታት መካከል ከ1703-1708 ዓ.ም ለአምስት ዓመታት በንግሥና የቆዩት ከዐፄ ዮስጦስ ጀምሮ ነው፡፡ አድርሽኝ የተሰኘው ሥርዓትም በእርሳቸው ተጀምሯል፡፡

ዐፄ ዮስጦስ የአድያም ሰገድ ኢያሱ የእህት ልጅ ፣ የፃድቁ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ደጃዝማች ድል በኢየሱስ ይባላሉ፣ እናታቸው በውል አይታወቁም፡፡ ዐፄ ዮስጦስ የጎንደር ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን የተከሉ እና በጥምቀት ጊዜ እመቤታችን የተገለፀችላቸው ንጉሥ ናቸው፡፡ ዐፄ ዮስጦስ በንግሥናቸው ወቅት ከሱዳኖች ጋር በነበራው ግንኙነት ሱዳኖች አንገብርም እያሉ ያስቸግሯቸው ነበር፡፡

ቱርኮች እና ግብጾች እየመጡም ሱዳኖችን አትገብሩ እያሉ ይሰብኳቸው ነበር፡፡ በአብርሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ሱዳኖች አንገብርም እያሉ በነበረበት ወቅት አብርሐ ወአጽብሐ ሒደው 5000 ግመል አመጡ እየተባለ ይነገርላቸዋል፡፡

በዐፄ ዮስጦስ ንግሥና ዘመንም ሱዳኖች አንገብርም በማለታቸው ንጉሡ ቸር አድርሰሽ ድል አድርጌ የመለስሽኝ እንደሆነ በየዓመቱ እዘክራለሁ ብለው ተስለው (ብጽዓት ገብተው) ወደ ጦርነቱ ሄዱ፡፡ ድል አድርገው ከተመለሱ በኋላ ሱባኤ ፍልሰታን ማታ ማታ መኳንንቱን ሰብስበው መዘከር ጀመሩ፡፡ ስያሜውንም €œአድርሽኝ€ በማለት ሰየሙት፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጎንደር ሊቃውንት በየዓመቱ እንዲደረግ ወሰኑ፡፡ እሰከዛሬም ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ቀጥሏል፡፡ አድርሽኝ በእቴጌ ጣይቱ ዘመን ወደ ሸዋ (አዲስ አበባ) መሄዱንና ወደ ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች በእቴጌ ጣይቱ ጊዜ መስፋፋቱን የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት መጋቤ ምሥጢር መምህር ተሾመ ታደሰ በሐመረ ኖኅ ሠለስቱ ምዕት ጉባኤ ቤት የመጽሐፈ መነኮሳት መምህር የታሪክ መጻሕፍትን በመጥቀስ ይገልጻሉ፡፡

፪.ሥርዓተ አድርሽኝ
1.በአጥቢያው በተመረጠ ምእመን ቤት፡-
የአድርሽኝ ሥርዓት በአጥቢያው በተመረጠና በእድሜ ትልቅ የሆነ፤ በሃይማኖቱ፤ እንዲሁም በሥነ ምግባሩ የተመሰከረለት ሰው ቤት ተመርጦ ይደረጋል፡፡

ከሐምሌ 30 ቀን ምሽት ጀምሮ ምእመናን ተሰባስበው በአባታችን ሆይ ጸሎት ሥርዓቱ ይጀመራል፡፡ ቆሎ፣ ዳቦ፣ ጠላ ይዘጋጃል፡፡ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ጽዋ ይጠጣሉ። በተለይም መነኮሳይያት እናቶች በሚታደሙበት ጽዋ ላይ €œኦ! ማርያም የሚለውን የተማጽኖ መዝሙር ይዘምራሉ።

ማታ (ሌሊቱን ሙሉ) እሳት እያነደዱ መዝሙር በተመስጦ ይዘመራሉ፡፡ መዝሙሩም እንደ ውዳሴ ማርያም ማታ ማታ ይደረሳል፡፡

ባለ ተራው ሰው ቁሞ ያስተናግዳል፡፡ ከአንዱ ሰው ቤት ሱባኤውን አብረው ካሳለፉ በኋላ የባለፈው ዓመት ሥዕለት መዝገብ ወጥቶም እየተነበበ እንዲያስታውሱት ይደረጋል፤ ሥዕለቱም ይሠበሠባል፡፡ ለ16 ብቻ ይህን የተሰበሰበውን ሥዕለት ለበዓሉ የሚሆን የሚያስፈጽም ጊዜያዊ ኮሚቴ ይመረጣል፡፡ በ16 ሁሉም ሰው አብሮ ያሣተፋል፣ ይመገባል፡፡

በ16 ባራኪ ካህን ይጠራል፣ ካህኑ ይባርካል ድግሱ ይጀመራል፡፡ በዚህ ወቅት የቆሎ ተማሪዎችም ይጠራሉ፡፡

ሣር ተጎዝጉዞ ወንዱ ለብቻ ሴቱ ለብቻ ሆነው ለ15 ቀን ይተኛሉ፡፡ ሣሩን ከነሐሴ 16 ቀን ኪዳነ ምሕረት ክብረ በዓል በኋላ ያቃጥሉታል፡፡

በየቤቱ ያሉ ልጆች ሁሉ እንደየእድሜአቸው ተቀምጠው በሥርዓቱ ይሳተፋሉ፡፡

የዕድሜ ባለጸጋ አባቶች እና እናቶች መርቀው ለሚቀጥለው ዓመት ሥዕለት መሳል ተለመደ ነው፡፡ ሰውም እንደየአቅሙ ይሳላል፡፡

በአድርሽኝ ወቅት የተጣላ ካለ ይታረቃል፡፡

2.በሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች
የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጧት ጧት የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዓ ማርያም እና መልክዓ ኢየሱስ በሕብረት ያደርሳሉ፡፡

ማታ 11፡00 ጀምሮ ደግሞ ፍልሰታን የሚመለከት መዝሙር፣ ትምህርት፣ ሥነ ጽሑፍ በቅደም ተከተል ቀርበው የተዘጋጀው ኅብስት እና ቆሎ ይበላል፡፡

የሰንበት ተማሪዎች ከዚህ በታች የተጠቀሰውን የእናቶች የምሕላ ዝማሬ ይዘምራሉ፡፡
ኦ!ማርያም
ኦ!ማርያም እለምንሻለሁ ባሪያሽ፤
እስኪ አንድ ጊዜ ስሚኝ ቀርበሽ፤ ከአጠገቤ ቆመሽ፤
ፅኑ ጉዳይ አለኝ ላንቺ የምነግርሽ፤
የዓለሙን መከራ ያየሽ፤
በእናትሽ በአባችሽ ሀገር፤
በምድረ ግብፅ ዞረሽ ውሃ የለመንሽ፡፡
ከሁሉ ሁሉ ጤፍ ታንሳለች፤
ከጭቃ ወድቃ ትነሳለች፤
ስትነሳ /2/ የአዳም ልጅ ሁሉ ሞትን ረሣ፤
የአዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና የኑሮ ቤቱን ረሣና፤
ተው አትርሳ /2/ ተሠርቶልሃል የእሳት ሳንቃ፡፡
ያን የእሳት ሳንቃ፤ የእሳት በር፤
እንደምን ብዬ ልሻገር፤
ተሻገሩት አሉ የሠሩ ምግባር፤
እኔ ባሪያሽ እንዴት ልሁን? ሰላም ሰጊድ /2/
በመሥቀሉ ሥር ያያትን ተሰናበታት እናቱን፤
እናትዬ ለምን ታለቅሻለሽ ተሰቅዬ፤
ይስቀሉኝ ሐሰት በቃሌ ሣይገኝ፡፡
ንፅሕት የወልደ እግዚአብሔር እናት፤
ንፅሕት በፍቅሯ ወዳጆቿን ስትመራ፤
ንፅሕት በቀኝ ወዳጆቿን ስትጎበኝ፤
የእኛስ እመቤት ያች ሩኅሩኅ፤
ከለላችን ናት እንደ ጎጆ፤
እርሷን ብለው ጤዛ ልሰው ኖሩ ትቢያ ለብሰው /2/
ኪዳነ ምሕረት ሩኅሩኅ ተይ አታቁሚኝ ከበሩ፤
የገነሃም እሣት መራራ ነው አሉ፤
እኔ ባሪያሽ እንዴት ልሁን? ሰላም ሰጊድ /2/
ድንግል ማርያም ንፅሕት፤
የምክንያት ድኅነት መሠረት፤
እንለምንሻለን ወደ አንቺ አንጋጠን፤
ከፈጣሪ በይ አማልጅን ሰላም ሰጊድ /2/
ኃያል /2/ ቅዱስ ሚካኤል ኃያል፤
የለበሰው ልብሱ የወርቅ ሐመልማል፤
ይህም ተጽፏል በቅዱስ ቃል ሰላም ሰጊድ /2/
ጊዮርጊስ ስልህ ዘንዶ ሰገደ ከእግርህ፤
እፁብ ድንቅ ይላሉ ገድልህን የሰሙ፤
አንተ አማልደኝ ከባሥልጣኑ ሰላም ሰጊድ /2/
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ደግ አባት፤
መጥቼልሃለሁ ከደጋ፤
ስንቄንም አድርጌ አጋምና ቀጋ፤
አንተ አማልደኝ ከፈጣሪ ሰላም ሰጊድ /2/
ፃድቅስ ባያችሁ ተክለ ሃይማኖት፤
በአንድ እግር ቆመው ሰባት ዓመት፤
በተአምኖ ሰባት ባቄላ ምግብ ሆኖት /2/
ተክለ ሃይማኖት አባቴ፤
መሠላሌ ነህ ለሕይወቴ፤
የዓለሙን ኑሮ መጥፎነቱን፤
የፈጣሪያችን ቤዛነቱን፤
አስተውለኸው አጥንተኸው፤
ደብረ ሊባኖስ የተሰዋኸው፡፡
ክርስቶስ ሠምራ እናታችን፤
ከአምላካችን ፊት መቅረቢያችን፤
ሣጥናኤልን አሸንፈሽ፤
ከግዛቱ ውስጥ ነፍስን ማረክሽ፡፡
ክርስቶስ ሠምራ ቅድስቷ፤
ለጽድቅ ሕይወት አማላጇ፤
እንለምንሻለን ወደ አንቺ አንጋጠን፤
ከፈጣሪ በይ አማልጅን ሰላም ሰጊድ /2/
ኦ! አባቴ አንተ ረኃቤ ነህ ጥማቴ፤
የኔ መድኃኒት ኃያል ተመልከተን ዝቅ በል፤
የነገሩህን የማትረሳ፤
የለመኑህን የማትነሳ፤
አምላኬ አንተ ነህ አምባዬ፤
የሕይወት ብርሃን ጋሻዬ፡፡
ማርያም ስሚን ወደ ሕይወት መንገድ ምሪን፤
ከአጠገባችን ቁጭ ብለሽ አድምጭን፤
ይደረግልን ልመናሽ ስትመጪ /2/
አንቺ እናቴ ሆይ /2/ የሄድሽበትን ትቢያ ቅሜ፤
ያረፍሽበትን ተሳልሜ፤
በሞትኩኝ /2/ የኋላ ኋላ ላይቀር ሞት፡፡ /2/
በመጨረሻው ቀን በነሐሴ 16 የዛሬ ዓመት በሰላም ካደረስሽኝ እያሉ ሁሉም ሰው ሥዕለት ይሳላል፡፡
፫.አድርሽኝ ሃይማኖታዊ አንድምታው
አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ €œበእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሏል፡፡/ዮሐ. 7፡38/ እንዲሁም እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል” በማለት እርሱን ያመኑ እና በጸጋ ላይ ጸጋ እስኪሰጠው የከበሩ ወዳጆቹ እግዚአብሔር የሚሰጠው ጸጋ እና በረከት እንዲሁም ሕይወት በእነርሱ አማካኝነት ሲሰጥ የሚኖር መሆኑን ይገልፃል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ያለው በእኔ የሚያምን ለራሱ ብቻ ጠጥቶ ይረካል ሳይሆን “የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል€œ ነው፡፡ ውኃ የሚቀዳው እና የሚጠጣው ከምንጩ እንደሆነ ሁሉ የእግዚአብሔር በረከት የሚቀዳው ከጸጋው መቅጃዎች ከቅዱሳን ነው፡፡

ሰው ውኃ ሲፈልግ ወደ ምንጩ መሔድ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እግዚአብሔር የሚሰጠውን የሕይወት ውኃ የሚፈልጉ ሰዎችም ሊጠጡና ሊረኩ የሚችሉት እግዚአብሔር ጸጋውን ወደሚሰጥባቸው ወደ ቅዱሳን በመቅረብ ነው፡፡

ቅዱሳን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከቤቱ ጀምሮ በጽላቱ በጠበሉ ይታሰባሉ፡፡ እንደዚሁ ሁሉ በጎንደር ከተማ አንድ ትልቅ ታሪካዊ ትውፊት አለ እርሱም €œአድርሽኝ የተሰኘ ሲሆን በጾመ ፍልሰታ ወቅት የሚደረግ ሥርዓት ነው፡፡ ለዛሬ ዓመት አድርሽኝ፣ ለአዲሱ ዓመት አድርሽኝ እንደ ማለት ነው፡፡

አድርሽኝ መነሻው የሐዋርያት ሱባዔ ነው፡፡ በአንድ ቤት የመሆኑ ምሥጢር ሐዋርያት በአንድ ቤት ሆነው ሱባዔውን ያደርጉ ነበርና፡፡ አድርሽኝ ብፅዓት /ሥዕለት/ ነው፡፡ አድርሽኝ ተስሎ የሚያፍር የለም ታደርሳለች፡፡ ሁሉም በፍልሰታ ወቅት አንቃዕድዎ ኅሊናውን ወደ እመቤታችን ያደርጋል፡፡

ምንጭ፡-መጋቤ ምጢር መምህር ተሾመ ካሴ በሐመረ ኖኅ ሠለስቱ ምዕት ጉባኤ ቤት የመጽሐፈ መነኮሳት መምህር; የቃል አስረጅ እና የሰንበት ት/ቤት መረጃዎች

No comments:

Post a Comment