መስከረም 7 ቀን 2008 ዓ.ም
ምንጭ፡ ማኅበረ ቅዱሳን http://eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1995-2015-09-18-18-35-44
ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ /ከጎንደር ማእከል/
ነገርግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው ወንድሙንም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?፡፡1ኛ. ዮሐ. 3፡17
መንፈሳዊ በዓላትን መንፈሳዊ ይዘታቸውን ጠብቆ ከማክበር ባለፈ የተቸገሩ ወገኖችን ማስታወስና መጎብኘት ሃይማኖታዊ ግዴታ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት ስትሰብክ ኖራለች ወደፊትም ትቀጥላለች፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ይህንን መሠረት በማድረግ በየበዓላቱ ነዳያንን በመጎብኘት፤ አብሮ በዓላትን በማክበር ችግሮቻቸውን በመጋራት ድጋፍ ያድርጋል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለፍርድ ሲመጣ የሚጠይቀን ይህንኑ ክርስቲያናዊ ተግባር በስሙ መፈጸማችንን እንደሆነ በወንጌል አስቀምጦልናል፡፡ እውነት እላችኃለሁ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳን ስላደረገችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል፡፡ማቴ25፡40
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል የጎንደር ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ የ2008 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓልን ምክንት በማድረግ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም በደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን በግቢ ጉባኤው ራእየ ምንትዋብ አዳራሽ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ለ4ኛ ጊዜ ከ500 ነዳያን ጋር አክብሯል፡፡
ግቢ ጉባዔው ከተመሠረተ 24 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታትም ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲፈጽም ቆይቶአል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው ነዳያንን በበዓላት የማስታወስ መርሐ ግብር ነው፡፡
መርሐ ግብሩ የተጀመረው በትምህርት ምክንያት በክረምት በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ የሚቆዩና አዲስ ዓመትን ግቢ ውስጥ በሚያሳልፉ የሕክምና ተማሪዎች ነው፡፡ በወቅቱ ተማሪዎቹ ለምን ብቻችንን እናከብራለን? ለምን ከነዳያንን ሆነን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አናከብርም በማለት በ2005 ዓ.ም ላይ 120 ነዳያንን በማሰባሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ በደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተከበረ፡፡
ዓላማው ብራብ አብልታችሁኛል እና የሚለውን አምላካዊ ቃል ለመፈጸም፣ በዓላትን ከነዳያን ጋር አብሮ የማክበርን ልምድ ለማስቀጠል እና ደጋፊ የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት ታስቦ የተከናወነ ነው፡፡ ይህ አገልግሎት በየዓመቱ ቀጥሎም የ2008 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓልን በደመቅ ሁኔታ ከ500 ነዳያን ጋር አክብሯል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፤ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና ሠራተኞች፣ የአብነት መምህራን እና ተማሪዎች፣ እንዲሁም የደብሩ ሰባካ ጉባኤ አባላት ተገኝተዋል፡፡
ጸሎተ ወንጌል፣ የግቢ ጉባኤው መልእክት፤ ትምህርተ ወንጌል፣ ቡራኬ እና ቃለ ምዕዳን በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ ለነዳያን የምሳ ማብላትና የአልባሳት ስጦታ መርሐ ግብር በቅደም ተከተል ተከናውነዋል፡፡
 ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በሰጡት ቃለ ምዕዳን በዓሉን ከነዳያን ጋር ማክበራችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው፡፡ በዕለተ ምጽዓት ጊዜም የምንጠየቀው ይህንን ጥያቄ ነው በማለት ግቢ ጉባኤው አሰታዋሽ የሌላቸውን ነዳያን በማሰባሰብ ላደረገው አርአያነት ያለው አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አልባሳትን ጨምሮ ገቢው የተገኘው ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ሠራተኞች፣ ከበጎ አድራጊዎችና እና ከከተማው ምእመናን ነው፡፡
ዩኒቨርስቲው እና ክፍለ ከተማው ለነዳያን ማመላለሻ መኪና በመመድብ፣ ነዳያንን ከያሉበት በማሰባሰብ፤ እንዲሁም የደብሩ አሰተዳደርና ሰባካ ጉባኤ ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
መርሐ ግብሩም በጎንደር ፋና ኤፍ ኤም 98.1 የሚዲያ ሽፋን አግኝቷል፡፡
በየዓመቱም ይህ መርሐ ግብር የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ግቢ ጉባኤው ከነዳያን ጋር በዓሉን አብሮ ማክበር ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸገሩበት ያለውን የመጠለያ ችግር ለመፍታት ፕሮጀክት ተነድፎ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱም ከጎንደር ልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የቁሳቁስ እና የቦታ ድጋፍ አግኝቷል፡፡
|
No comments:
Post a Comment